image
image
image
image

የ2017 ዓ.ም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና የማስፈጸሚያ ሰነድ የጋራ ተደረገ።

ግንቦት 11, 2017
የልደታ ክ/ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ለወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ለክ/ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ባለሙያዎች የከተማ አቀፍ ፈተና የማስፈጸሚያ ሰነዱን አስተዋውቋል። የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሠፋ ግርማ በንግግራቸው እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ስናስፈትን በጥንካሬም፣ በክፍተትም የተገለጹ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ገልጸው በተለይ በክፍተት የተገለጹትን ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት ያስፈልጋል ብለዋል። በጽ/ቤቱ የቡድኖች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ገዳ ሞሲሳ በበኩላቸው የ2017 ዓ.ም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ፣ ክፍተቶችንና ስህተቶችን ለመቀነስ በዋናነት ደግሞ ተማሪዎች የተሻለ ዝግጅት አድርገው ፈተናውን እንዲፈተኑ ለማድረግ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው መረጃ አሞላል ላይ የጾታ ስህተት፣ የስም ስህተት እንዲሁም የፊደል ግድፈት ካለ ከወዲሁ መስተካከል ይኖርበታል ብለዋል። በጽ/ቤቱ የፈተናዎች አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ ኑረዲን ሶማ በ2016 ዓ.ም በተሠጠው ከተማ አቀፍ ፈተና ላይ በፈተና ጣቢያ ኃላፊዎች፣ በፈታኝ መምህራን፣ በሱፐርቫይዘሮች እንዲሁም በአስፈታኝ ት/ቤቶች ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች መኖሩን ገልፀው የፈታኞች መዘግየት፣ የፈተናዎች መደበላለቅ፣ የተማሪዎች መረጃ በጥንቃቄ አለመሙላት፣ የተማሪዎች ፎቶግራፍ መቀያየር፣ ለተፈታኝ ተማሪዎች በቂ ግንዛቤ አለመስጠት፣ ወዘተ... ከተስተዋሉ ክፍተቶች መካከል መሆናቸውን አቶ ኑረዲን የገለጹ ሲሆን እነዚህ ስህተቶች በ2017 ዓ.ም እንዳይደገሙ ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል። የ2017 ዓ.ም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና የማስፈጸሚያ ሰነዱንም አቅርበው ውይይት ተደርጓል። በ2017 ዓ.ም በልደታ ክ/ከተማ በከተማ አቀፍ ፈተና ላይ በሁለቱም መርሃ ግብሮች የ8ኛ ክፍል 3031 ተማሪዎች፣ የ6ኛ ክፍል 3664 ተማሪዎች በ12 የመፈተኛ ጣቢያዎች ለፈተና የሚቀመጡ ይሆናል።

መልዕክትዎን ይላኩ

ሌሎች ዜናዎች